ሐሙስ 13 ማርች 2014

የነዳጅ ፍለጋ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እያሳዩ ነው - የማዕድን ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 2 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉት የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋዎች ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩባቸው መሆኑን የኢፌዴሪ የማዕድን ሚኒስቴር ገለፀ።
የማእድን ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ሻጊ እንዳሉት፥ በፍለጋዎቹ እየተገኙ ያሉት መረጃዎች የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብቶች እንደሚገኙ የሚጠቁሙና ተስፋ ሰጪዎች ናቸው።
የክምችት መጠንን በተመለከተም የተገኙት መረጃዎች እንዲሁ መልካም ውጤት ሊገኝ እንደሚችል የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት 13 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የነዳጅ ፍለጋ ፈቃድ አውጥተው እየሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ ሁለቱ ቀጥታ ወደ ቁፏሮ ገብተው የክምችት መጠኑን በማጥናት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ቀሪዎቹ የመሬት ላይ ጥናት በማድረግ ላይ ሲሆኑ በቅርቡም ወደ ቁፋሮ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በደቡብ ኦሞ ቁፋሮ እያካሄደ የሚገኘው አፍሪካ ኦይል እስካሁን በአከባቢው እስከ 2 ሺህ 850 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር የክምችት መጠኑን እያጠና እንደሚገኝ ነው አፍሪካ ሪቪው የዘገበው።

የመከላከያ ሰራዊት የሎጂስቲክ መምሪያ ኃላፊ ቤታቸው ሞተው ተገኙ

ፖሊስ የአሟሟታቸውን መንስኤ አጣራለሁ ብሏል
ሰላም ገረመው
የመከላከያ ሰራዊት የሎጂስቲክ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ተ/ሚካኤል ተስፋይ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸውን ፖሊስ
ጠቆመ፡፡ ሌተናል ኮሎኔሉ መደበኛ ስራቸውን አከናውነው ወደ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ከልጆቻቸው ጋር እራትበልተው መተኛታቸውን ምንጮች ገልፀው፤ ሌሊት ላይ ድምፅ እንዳሰሙና ልጆቻቸው ደርሰው ሲያዩዋቸው ሞተው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጎረቤቶች ተደናግጠው ኮሎኔሉን ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል ቢወስዷቸውም ህይወታቸው ቀድሞ በማለፉ የጦር ሃይሎች ሆስፒታል የኮሎኔሉን አስክሬን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አማካኝነት ለምርመራ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ልኳል፡፡
ሌተናል ኮሎኔል ተ/ሚካኤል ተስፋይ እድሜያቸው ለአቅም አዳም ካልደረሰ ሁለት ልጆቻቸው ጋር ይኖሩ እንደነበረ የታወቀ ሲሆን ባለቤታቸው በአገር ውስጥ እንደሌሉ ተጠቁሟል፡፡ ፖሊስ የኮሎኔሉን የሞት መንስኤ ለማጣራት የህክምና ምርመራ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል፡፡

በታላቁ ሩጫ የተሳተፉ አባሎቼ ታሠሩ ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ከሰሰ

የትላንት በስቲያውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መታሰቢያ ተንተርሶ በተሠናዳው ታላቁ ሩጫ “ሃሳባቸውን ለመግለጥ” የወጡ ያላቸው አባሎቹ ለእስር ተዳረጉ ሲል፤ ሰማያዊ ፓርቲ ወነጀለ።

ይበልጡን የፓርቲው አባልና የአመራር አባል የሆኑ ወጣት ሴቶች የሚገኙባቸው በርካቶች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ነው፤ ሰማያዊ ፓርቲ ያስታወቀው።

በእንቅስቃሴው በመሳተፋቸው ብቻ የደምብ ልብስ በለበሱ ፖሊሶችና እንዲሁም የሲቪል ልብስ በለበሱ የደህንነት ሠራተኞች ለአጭር ጊዜ ተይዘው ከቆዩ በኋላ፥“ሁከትና ሽብር እያነሳሳችሁ፤” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውን የፓርቲው የሴቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ወ/ሪት ኢየሩሳሌም ተሥፋው።

ፓስተሩ ሴቶች ፓንት እና ጡት መያዣ እንዳያደርጉ አገዱ

በ ናይሮቢ ኬንያ የሚገኘው ሎርድስ ፕሮፔለር ሪዴምሽን ቸርች ፓስተር የሆኑት ሬቨረንድ ንጆሂ፣ ወደሳቸው ቸርች የሚመጡ ሴቶች ፓንት እና ጡት መያዣ እንዳያደርጉ አገዱ፡፡
“ሰው ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ነጻ መሆን አለበት” ያሉት ፓስተሩ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ለመቀራረብና መንፈስ ቅዱስም በውስጣቸው እንዲገባ ፓንትና ጡት መያዣ አድርገው መጨናነቅ የለባቸውም ስለዚህ በኔ ቸርች ይህ ታግዷል” ማለታቸውን ናይጄሪያን ዎች፣ ኬንያን ፖስት እና ሌሎችም ጋዜጦች የካቲት 24 (ማርች 3) ዘግበዋል። አንዳንዶች ይህን ተግባር የመጨረሻው ዘመን ምልክት ሲሉ ተቃውመውታል።
ከአንድ ወር በፊትም እዚህ አሜሪካ፣ ቨርጂኒያ የሚገኘው ዋይት ቴል ጸሎት ቤት፣ የራቁት አምልኮ መጀመሩንና እዚያ የሚመጡ ሁሉ ራቁታቸው መሆን እንደሚችሉ ማስታወቁን እንዲያውም ፓስተሩ፣ ፓስተር አለን ራሳቸው ሙሉ በሙሉ ራቁታቸውን ሆነው እንደሚሰብኩ በአሜሪካ ሚዲያዎች መዘገቡ የሚታወስ ነው።

የሀረር ከተማ ገበያ መደብሮች ላይ ለአምስተኛ ጊዜ ከፍተኛ ቃጠሎ ደረሰ

ለፈዉ እሁድ በሐረር ከተማ ሸዋ በር የገበያ ማእከል ለአምስተኛ ጊዜ በደረሰዉ ቃጠሎ ከ700  በላይ የንግድ መደብሮች ወድመዋል። ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በስልክ ስለ ቃጠሎዉ የገለጹ አንዳንድ የንግድ ባለቤቶች በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ብር የሚገመት ኪሳራ እንዳደረሰ ተናግረዋል። መንግስት እሳቱ የተነሳዉ ከአንድ የተዘጋ ምግብ ቤት ዉስጥ ነዉ፤ ይላል። ባለንብረቶቹ ግን የእሳቱ መንስኤ ምን እንደሆነ እስካሁን በግልጽ አይታወቅም።

እሳቱ ልክ እንደተነሳ ተመልካቾች ለፖሊስ ቢያሳዉቁም ቃጠለውን ከማጥፋት ይልቅ ተኩስ እያሰሙ ሊያጠፋ የተሰበሰበዉን ሕዝብ መበተን መርጠዋል፤ ሲሉ ከሰዋል። መደብሮቹ ለስምንት ሰዓታት ከነደዱ በኋላ አንዲት አነስተኛ የእሳት አደጋ መከላከያ እንደደረሰች፤ ወዲያዉ እንደጠፋም መንግስት ለግንባታ ቦታዉን በቡልዶዘር መቆፈር እንደ ጀመረ ንብረቴ ወደመ ከሚሉት አንዱ አቶ ገብረ መድህን ገብረ መስቀል ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በስልክ ገልጸዋል። የሀረሪ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወ/ሪት ሐሰናት አቡበከር በሌላ በኩል እሳቱ የተነሳዉ ከምግብ ቤቱ ዉስጥ መሆኑን የፌዴራሉና የክልሉ ፓሊሶች አረጋግጠዋል፤ ይላሉ።

ከቃጠሎዉ ጋር ተያይዞ በተነሳ ግጭት ከ200 በላይ ሰዎች በፖሊሶች ታስረዉ እንደነበር፥ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድርስም፥ ለአሜሪካ ድምጽ በቀዉሱ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት ባለ ሃብት አቶ ገብረ-መድህን ገብረ-መስቀልን ጨምሮ ቁጥራቸው 150 የሚደርስ ሰዎች እስር ላይ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ጠቁመዋል።  የክልሉ መንግስት ግን አቶ ገብረ መድህን የታሰሩት ንብረት በመዝረፍ ተጠቁሞባቸዉ ነዉ፤ ግጭት ሲካሄድ አዉቶቡስ የሰበሩ ሶስት ሰዎች ብቻ ታስረዋል፤ ብሏል። ረቡእ እለት የሀረሪ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ሙራድ አብዱል ከሪም ንብረታቸዉ ከወደመባቸዉ ሰዎች ጋር ተገናኝተዉ፣ ሱቆቻቸዉን መልሶ ለመገንባት መሬትና ብድር እንደሚሰጣቸዉ መግለጻቸው ተዘግቧል።