ዓርብ 27 ዲሴምበር 2013

በጥንቆላ ተግባር ተሰማርቶ የነበረው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ





አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 16 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከህመም አድናለሁ ፣ ከደባል ሱስ እገላግላለሁ እና ሌሎች መሰል ድርጊቶችን እፈፅማለሁ በማለት በጥንቆላ ተግባር ተሰማርቶ ከተለያዩ ሰዎች ጥሬ ገንዘብና ወርቅ ያጭበረበረው ግለሰብ በ8 ዓመት እስራት ተቀጣ።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ውንጀል ችሎት በተከሳሹ ተፈሪ ንጉሴ ላይ የ8 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም አስተላልፎበታል።
በቡራዩ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ39 ዓመቱ ንጉሴ ታህሳስ 14 ቀን 2005 ዓ.ም  ወይዘሮ መሰረት ታዬ የተባሉትን የግል ተበዳይ አሁን ካንቺ ጋር ያለው ሁለተኛ ባልሽ  ጥር 30 ቀን ይሞታል ፥ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን 300 ሺህ ብር  ስጪኝና ከሞት ላድነው በማለት 130 ሺህ ብር የግል ተበዳይ ለመስጠት በመስማማት ብሩን እንደወሰደ የአቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል።
በተጨማሪም ከተበዳይ ወይዘሮ መሰረት ላይ የጆሮ እና የአንገት ወርቅም እንደወሰደ በክሱ ተካቷል።
በተመሳሳይ ወይዘሮ አፀደ ስንታየሁን ባልሽ ካለበት ደባል ሱስ አላቅቀዋለሁ በማለት ለማሳመኛ የተለያዩ የማሳሳቻ ድርጊቶችን በመጠቀም 50 ሺህ ብር እና 21 ካራት የሆነ 8 ግራም የወርቅ የአንገት ሃብል መውሰዱንም አቃቤ ህግ ለችሎቱ በክሱ አስረድቷል።
3 ተበዳይ ከሆኑት ወይዘሮ አመናይ ከበደን ከህመምሽ እፈውስሻለሁ በማለት ካልተያዘ ግብረ አበሩ ጋር 100 ሺህ ብር እና 76 ግራም የተለያዩ  መጠን ያላቸው ወርቆችን በድምሩ 161 ሺህ 200 ብር ወስዷል ሲልም አቃቤ ህግ በክሱ አካቷል።
በአቃቤ ህግ በ3 የማታለል ክሶች የተመሰረተበት ተፈሪ ንጉሴ ያቀረበው የመከላከያ ማስረጃ የቀረበበትን ክስ ጥርጣሬ ውስጥ መክተት ባለመቻሉ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ውንጀል ችሎት ጥፋተኛ  ሲል  በ8 ዓመት እስራት ቀጥቶታል።
በጥላሁን ካሳ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ